ምክር ቤቱ በ6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤው የረቀበለትን የ2018 በጀት 53.9 ቢሊዮን ብር አፀደቀ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በ6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤው የክልሉ መንግስት የ2018 የስራ ዘመን በጀት 53 ቢሊዮን 911 ሚሊዮን 616 ሺህ 681 ብር እንዲሆን አፅድቋል።
በክልሉ ምክር ቤት የፕላን መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች አቶ እንቁ ዮሐንስ የበጀት ረቂቁን ለምክር ቤት አባላት በዝርዝር አቅርበዋል።
በመሆኑም የክልሉ መንግስት የ2018 የስራ ዘመን አጠቃላይ በጀት 53 ቢሊዮን 911 ሚሊዮን 616 ሺህ 681 ብር መሆኑን በመግለፅ የምክር ቤት አባላት እንዲያፀድቁም የተከበሩ አቶ እንቁ ዮሐንስ ጠይቀዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ተፈሪ አባተ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት የበጀት መግለጫ የክልሉን ኢኮኖሚ ፈጣን ዕድገት እንዲቀጥል የሀብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ እንዲሆንና ለድህነት ቀናሽ ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
ከፌደራል መንግስት ግምጃ ቤት ለ2018 በጀት ዓመት ጥቅል የበጀት ድጋፍ 22 ቢሊየን 68 ሚሊዮን 344 ሺህ 356 ብር፣ ከውጭ እርዳታ 59 ሚሊዮን 72 ሺህ 325.41 እንዲሁም ለዘላቂ ልማት ግቦች ማሳኪያ 984 ሚሊየን 200 ሺህ ብር በጀት ድጋፍ መገኘቱንም ኃላፊው አብራርተዋል።
የበጀቱ 20 በመቶ ለክልል ማዕከል እንዲሁም 80 በመቶ የሚሆነውም ለዞን እና ለሪጂዮ ፖሊስ ከተማ አስተዳደሮች የተደለደለደ መሆኑንም አቶ ተፈሪ አብራርተዋል።
ለካፒታል የተያዙ በጀቶች በአብዛኛው የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የበጀቱ 57.6 በመቶ በውስጥ ገቢ የሚሸፈን ሲሆን 43.4 በመቶ በፌደራል መንግስት ድጎማ እንደሚሸፈንም ተገልጿል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች በርካታ ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልፀው ይህን ለማሳካት የውስጥ ገቢን አሟጦ መሠብሰብ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ መዋቅሮች በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ መዋቅሮች የህዝብ ተሳትፎን የበጀት አካል አድርገው ሊወስዱ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በዘንድሮው በጀት አመት ለመሠብሰብ የተያዘው የገቢ እቅድ እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የምክር ቤት አባላትም ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት የበጀት ክፍፍሉ ቀመርን መሠረት አድርጎ የተሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የተሰጠው ትኩረት አበረታች ነው ብለዋል።
በተለይ ለታችኛው መዋቅር የሚመደቡ በጀቶች ለታለመላቸው አላማ ብቻ እንዲውሉ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
የ2018 የስራ ዘመን በጀት 53 ቢሊዮን 911 ሚሊዮን 616 ሺህ 681 ብር እንዲሆን የምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE