በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጤናው ዘርፍ በ2017 ዓ.ም የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል የተናበበ ሥራ መከወን እንደሚያስፈልግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ
በዓመታዊ የጤና ሴክተር ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለሌሎች የልማት ሥራዎች ምቹ መደላድል በሚፈጥረው የጤና ልማት ዘርፍ ዓይነተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ይህንኑ ተልዕኮ መወጣት በቀጣይ ትልቅ የቤት ሥራ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይም የ3 ዓመት የጤናው ዘርፍ የመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
ከዕቅዱ ምሰሶዎች መካከል ጠንካራ የጤና ስርዓት መዘርጋት፣ ጠንካራ የጤና ተቋማት እንዲፈጠሩ ማድረግ፣ የሰለጠነ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራት፣ የጤና መረጃ ስርዓት ማዘመን እና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መፍጠሩ ላይ በትጋት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ጥላሁን ከበደ ጠቁመዋል።
የጤና የልማት ግብን ለማሳካት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እንደምቹ አጋጣሚ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት 2 ዓመታት የጤና ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ አፈጻጸም ትግበራ ላይ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በክልሉ አብዛኛዎቹ የጤና ልማት ዘርፎች አፈጻጸም የተሳካ ቢሆንም በአንጻሩ ደካማ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ዘርፎችና መዋቅሮች መኖራቸውም የቢሮው ኃላፊ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ቀጣዩ አንድ ዓመት የዕቅዱ ማጠቃለያ ምዕራፍ መሆኑን በመረዳት ድክመቶችን ለማረም የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ፈጥኖ ወደሥራ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመድረኩ መክፈቻ ለረጅም ዓመታት በትጋትና በታማኝነት ላገለገሉ የጤና ባለሙያዎች በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና እና በቢሮ ኃላፊ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE