"ፈጣንና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ግብርና ዘርፉን ማሻሻል ተቀዳሚ ተግባር ነው" ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የማስተዋወቅ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲውን ለማስፈፀምና ትግበራውን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ያለው የዘርፉ አመራር በፖሊሲው በቂ ግንዛቤ በመያዝ የማስተዋወቅ ስራ መስራት እንዲችሉና ለተግባራዊነቱ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መድረኩ እንደተዘጋጀ ገልፀዋል፡፡
ሀገራችን ወደ ለውጥ እንድትገባ ካደረጓት ገፊ ምክንያቶች አንዱ በኢኮኖሚ የገጠመን ስብራት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህ መፍትሄ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ መሆኑን ታምኖበት ተግባራዊ በመደረጉ በርካታ ተበጨባጭ ለውጦች መመዝገብ ችለዋል ብለዋል።
የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለችግሮቻችን ሀገራዊ መፍትሄን የሰጠ መሆኑንን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ በአረንጓዴ አሻራ፣ ስንዴ ከራስ አልፎ ወደ ውጪ መላክ በመጀመር የታሪክ እጥፋት እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ማበርከት ችሏል ሲሉ ገልፀዋል።
ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት ግብርና ግንባር ቀደም መሆኑን ገልፀው ያለንን የተፈጥሮና የሰው ሀይል ፀጋ በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ በማሻሻልና በማዘመን የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የምግብ ልዑላዊነትን ማስከበር ይገባል ብለዋል።
ይህንንም በተሻለ መንገድ ለመተግበርና አጠቃላይ የግብርናውን ሽግግር እውን ለማድረግ እንዲቻል አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መፅደቁን ገልፀው ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር ) ፖሊሲው እንደ ሀገሬ የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚያግዝ መሆኑንን ገልፀው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲው የቴክኒክ እና የፖለቲካ ሂደቶችን አልፎ የትግበራ ምዕራፍ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መነሻ ሀሳብ ላይ ግምገማ በማድረግ የተዘጋጀው ሰነድ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ችግሮችን እና የመፍትሄ ሀሳቦችን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑንን ገልፀዋል።።
Copyrights 2021. . All Rights Reserved.
Developed by NATNAEL ABATE